Categories
Amharic

የኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ የተዘጋጀ መግለጫ ሰኔ-4

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 6630 የላብራቶሪ ምርመራ አንድ መቶ ሰልሳ አራት (164) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2670 ደርሷል፡፡ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 117 ወንድ እና 47 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ 1 እስከ 92 ዓመት ውስጥ ይገኛል። በዜግነት መቶ ሰልሳ ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንዱ የውጭ ሃገር ዜጋ ነው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው አንድ መቶ አራት (104) ሰዎች ከአዲስ አበባ ፣ ሃያ ስድስት (26) ሰዎች ከሶማሊ ክልል ፣ ሃያ ሁለት (22) ሰዎች ከአማራ ክልል፣ አራት (4) ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ አራት (4) ሰዎች ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል፣ ሁለት (2) ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ አንድ (1) ሰው ከሐረሪ ክልል እንዲሁም አንድ (1) ሰው ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ናቸው።

በሀገራችን የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ከተገኘ ዛሬ ሶስተኛ ወሩን አስቆጥሯል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ብዛት 250 የነበረ ሲሆን ባለፈው አንድ ወር ብቻ 2420 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህም ማለት ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ጋር ሲነፃፀር በ10 እጥፍ ጨምሯል።

በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኙ መስፋፋት ግምት ወስጥ በማስገባት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል። መከላከል ከመታከም ይቀላል፣ ቤት መቆየት ሆስፒታል ከመተኛት ይሻላል፣ የአፍና የአፍንጫን መሸፈኛ አድርጎ መተንፈስ በማሽን ከመተንፈስ ይልቃል። ስለሆነም እነዚህን አንዲሁም ሌሎችን የመከላከያ መንገዶች ሳንዘናጋ በመተግበር እራሳችንን እና የምንወዳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በሽታ እንጠብቅ።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ የአምስት ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል። በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር አርባ (40) ደርሷል፡፡ በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡  ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ዝርዝር ሁኔታ እንደሚከለው ቀርቧል፡፡

ተ.ቁየመኖሪያ አድራሻጾታዕድሜማብራሪያ
1አዲስ አበባወንድ92በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘ
2አዲስ አበባወንድ58በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘ
3አዲስ አበባሴት80በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበሩ
4አዲስ አበባወንድ36በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበረ
5ሶማሊወንድ70በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበረ

በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት ሰላሳ አራት (33) ሰዎች (32 ከአዲስ አበባ እና 1 ከአማራ ክልል) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 434 ነው።

በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ

አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ165,151
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ6,630
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ164
በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው2194
በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር32         
አዲስ ያገገሙ33
በአጠቃላይ ያገገሙ434
በአጠቃላይ በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ40
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ2
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር2,670

የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡

በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡

ዶ/ር ሊያ ታደሰ

የጤና ሚኒስትር

ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *