Categories
Amharic

የኮቪድ- 19 የዴልታ ዝርያ በኢትዮጵያ ተገኘ

የኮቪድ ዴልታ ዝርያ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የጤና ሚኒስትር ክበርት ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ፣ ዴልታ ዝርያ መግባቱ ተረጋግጧል፡፡ የኮቪድ-19 የዴልታ ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት የሚችል፣ሰዎችን ለከባድ ህመም የሚዳርግ፣ለሞት የሚያበቃ አደገኛ ዝርያ እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልፀዋል። 

አዲሱ ዝርያ ሁሉንም የዕድሜ ክልል የሚያጠቃ፣ ለከባድ ህመምና ሞት የሚዳርግ በተለይም ባልተከተቡ ሰዎች ላይ የሚበረታ ዝርያ መሆኑን ክበርት ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል። የኮቪድ-19 ክትባትን ሕብረተሰቡ በየጤና ተቋማቱ በመገኘት እንዲወስዱ፣ የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም ተቋማትና ግለሰቦች እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች፣ የሚሞቱና ፅኑ ህሙማን ቁጥር በጣም ከፍ እንዳለ የጤና ሚኒስትር ክበርት ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልፀዋል። ባለፈው ሳምንት ብቻ 8 ሺህ 300 ሰዎች  በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲያዙ እስካሁን በአገሪቱ 313 ሺህ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። ከ4 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመያዝ ምጣኔውም ከ1 በመቶ ወደ 20 በመቶ አሻቅቧል፤ ባለፈው ሳምንት 118 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዲሱ የኮቪድ- 19 የዴልታ ዝርያ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ እያንዳንዱ ግለሰብ ፤ ቤተሰብ ፤ ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፤ የሐይማኖት ተቋማት ፤ ሲቪክ ማህበራት ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር ከዚህ በፊት ያደርገው ከነበረው በበለጠና በተጠናከረ ሁኔታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክን ሁልጊዜና በአግባቡ ማድረግ ፤ የእጅ ንፅህናን መጠበቅ ወይም ሳኒታይዘር መጠቀም፣ አላስፈላጊ መሰባሰቦችን መቀነስ እንደሚገባ ኢንስቲትዩት እያሳሰበ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ 8335 ወይም የክልል ነፃ የሰልክ መስመሮች በመደወል ማግኘት እንደሚችሉ እንገልፃለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *