በኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 በሽታ በድጋሚ አራት አሃዝ ያለው ቁጥር ሪፖርት ማድረግ ከ ጀመርንበት የካቲት 20/2013 ጀምሮ ኮቪድ-19 የሚገኝባቸው እንዲሁም ወደ ፅኑ ህሙማን መርጃ ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ከፍተኛ ቁጥር ማስመዝገብ ቀጥለናል።
በኢትዮጵያ እስከ ትላንትናው እለት ድረስ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 181,869 ግለሰቦች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ 600 ግለሰቦች ፅኑ ህሙማን መርጃ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡በዛሬው እለት ለኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በደረሰን መረጃ ብቻ 9 ያህል ግለሰቦች ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
በኮቪድ-19 በትላንትናው ዕለት 8,055 ግለሰቦች ናሙና የሰጡ ሲሆን 2,057 ግለሰቦች የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች 26 ያህሉ ወይም 25.5% ኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር በማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ (COMBAT) ወቅት አስመዝግበን አናውቅም ፡፡
በዚሁ ዕለት አዲስ አበባን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡ ክልሎችን ብናይ :-
*በአዲስ አበባ 6,314 ግለሰቦች ናሙና ሰጥተው 1,552 ግለሰቦች ወይም 24.6%
*በኦሮሚያ 659 ግለሰቦች ናሙና ሰጥተው 264 ግለሰቦች ወይም 40.1%
*በሲዳማ 232 ግለሰቦች ናሙና ሰጥተው 105 ግለሰቦች ወይም 45.3%ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
እስከ ትላንትናው ዕለት 600 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ቫይረስ ተይዘው በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ይህ ቁጥር ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያው ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።ከእነዚህም ውስጥ 81 ግለሰቦች በአርቴፊሻል ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ወደ ኮቪድ19 ህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 73 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
እስከ ትላንትናው እለት ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የገቡ፤በፅኑ ህክምና ማዕከል ድጋፍ ሲደረግላቸው ከነበሩት ግለሰቦችውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡት ክልሎችን ስንመለከት ፦
*በአዲስ አበባ 439
* በኦሮሚያ ክልል 67
*በሲዳማ ክልል 58 ግለሰቦች ወደ ፅኑ ህሙማን መርጃ ክፍል የገቡ እና በፅኑ ህክምና ማዕከል ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩ ናቸው፡፡
በኮቪድ-19 ቫይረስ ተይዘው ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል የፅኑ ህክምና ክፍል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥር እያሻቀበ ነው።ስለሆነም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኝ ግለሰብ ፤ ቤተሰብ ፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፤ የሐይማኖት ተቋማት ፣ ሲቪክ ማህበራት ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግ ፣ የእጃቸውን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንድንከላከል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪውን ያቀርባል።
#እንድናገለግልዎማስክዎንያድርጉ