በሀገራችን የኮቪድ-19 ቫይረስ ከተገኘባቸውውስጥ 39 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ ከተመዘገቡት የህይወት ህልፈቶች ውስጥ 37 በመቶ ያህሉ የምንወዳቸው እህቶቻችን እና እናቶቻችን ናቸው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ ሴቶች በኮቪድ-19 ከመታመም እና ህይወታቸው ከማለፍ ባለፈ፣ የኮቪድ-19 ዓለም ዓቀፍ ወረርሽኝ በሴቶች ላይ ያለው ተጽእኖ በቁጥር ለመለካት ከምንችለው በላይ ነው፡፡ በኮቪድ-19 ትምህርት ከመዘጋቱ ጋር ተያይዞ የሴቶች እና የህጻናት ጥቃት፣ ያለእድሜ ጋብቻ እንዲሁም እርግዝና ጨምሯል፡፡ በኮቪድ-19 ምክንያት የሚታመሙን ከመንከባከብ ጀምሮ፤ ሞትን ጨምሮ በማህበረሰብ ውስጥ የሚኖርን ማህበራዊ አኗኗር ዘይቤዎች ላይ መሳተፍ እና መስራት ለሴቶች የተጣለ ሀላፊነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሴቶችን ተጋላጭነት እንዲሁም የኮቪድ-19 ተጽእኖ ይጨምራል፡፡ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንድ ሴት በቤት ውስጥ ክፍያ ሳይኖረው በሚሰሩ ስራ ከምታሳልፈው ሰዓታት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በተጨማሪ 4.1 ሰዓታት በተጨማሪ በቤት ውስጥ ስራ እና እንክብካቤ ያሳልፉሉ፡፡ ይህ ጥናት ከዚህ በተጨማሪ በኮቪድ-19 ዓለም ዓቀፍ ወረርሽኝ ወቅት 243 ሚልዩን ሴቶች የጾታ ጥቃት እንደደረሰባቸውም አሳይቷል፡፡ የጤናው ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከሌላው የማህበረሰብ አባላት እና የተለያዩ ስራዎች ላይ ከተሳተፉ ሰዎች ይልቅ ለኮቪድ-19 ተጋላጭ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በጤና ሴክተር ላይ ከተሰማሩ ሰራተኞች 70 በመቶ ሴቶች መሆናቸው የጤና ሴክተሩን የሴቶች ተጋላጭነት ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህን እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች ኮቪድ-19 ሴቶች ላይ ያለውን ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳያዎች ናቸው፡፡
እናት ለልጆችዋ አስተማሪ ናት፤ እህት ለወንድምና እህትዎ ጠባቂ፣ የእናት ምትክ ናት፤ ሴት ልጅ ለማሕበረሰብዋ መሰረት ናት፡፡ ጥንቃቄ የሴት ልጅ ባህሪ ነው፡፡ በዚህ በኮቪድ-19 ዓለም ዓቀፍ ወረርሽኝ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የምናደርጋቸውን ጥንቃቄ በመተግበር ለማህበረሰቤ አርአያ እንዲሁም ለሌሎች በማስተማር የማሕበረሰብ ጤና ለመጠበቅ ሴቶች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዛሬው እለት በሚከበረው የዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን በመተግበር ለበሽታው ቁጥጥር የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናደርግ ያሳስባል፡፡
መልካም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን #እንድናገለግልዎማስክዎንያድርጉ