ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 2383 የላብራቶሪ ምርመራ አስራ ስድስት (16) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ሁለት መቶ አስር (210) ደርሷል፡፡ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ 7 ወንድ እና 9 ሴት እንዲሁም እድሜያቸው ከ20 – 60 ዓመት የሆኑ ናቸው። የመኖሪያ ቦታቸው አዲስ አበባ የሆኑት 13 ሲሆኑ፣ 1 ሰው ከአማራ ክልል (ወልድያ ለይቶ ማቆያ) እና 2 ከደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል (ወላይታ ሶዶ ለይቶ ማቆያ እና ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ) ይገኛሉ።
የዕለቱ ታማሚዎች የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የተጋላጭነት ሁኔታ | የታማሚዎች ቁጥር |
የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው | 2 |
በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው | 13 |
የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው | 1 |
ድምር | 16 |
የላብራቶሪ ምርመራው በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት፣ በአርማውር ሃንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት፣ በብሄራዊ የእንስሳት ጤና በሽታዎች ምርመራ ማዕከል፣ በኢትዮጲያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ፣ በአዳማ የህብረተሰብ ጤና ምርምርና ሪፈራል ላብራቶሪ፣ በነቀምት የህብረተሰብ ጤና ምርምርና ሪፈራል ላብራቶሪ፣ በአማራ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት (ባህር ዳር እና ደሴ) ፣ በደቡብ ብ/ብ/ሕ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት፣ በአዲስ አበባ አስተዳደር ላብራቶሪ፣ በአርሲ ዩኒቨርስቲ ላብራቶሪ፣ በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ላብራቶሪ፣ በጅማ ዩኒቨርስቲ ሜዲካል ሴንተር እና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ላብራቶሪ የተከናወነ ነው፡፡
በዛሬው ዕለት በፅኑ ህክምና ላይ የነበሩ የ65 ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ወንድ ኢትዮጵያዊ ህይወታቸው አልፏል ይህም በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር አምስት (5) ደርሷል፡፡ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለፁ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይመኛሉ፡፡
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት ሁለት (2) ሰዎች ከአዲስ አበባ ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ዘጠና ሰባት (97) ነው።
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 32,689 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 2383 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 16 |
በአጠቃላይ በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ከህክምና ውስጥ ያሉ | 106 |
በፅኑ ህክምና ላይ ያሉ | 0 |
አዲስ ያገገሙ | 2 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 97 |
በዛሬው ዕለት በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 1 |
በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 5 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 210 |
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መጨመርን ከግንዛቤ በማስገባት ሕብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ እንዲተገብር ያሳስባሉ። በበሽታው መያዛችን ዕለት-ተዕለት በምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚወሰን መሆኑን በማስታወስ ከሰዎች ጋር ሊኖረን የሚችሉ ግንኙነቶችን በመገደብ እና ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታዎች ላይ መገኘታችን አስገዳጅ በሚሆንበት ሁኔታ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) በማድረግ ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተው፣ አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንድንከላከል በጥብቅ እናሳስባለን።
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ግንቦት 1፣ 2012 ዓ.ም