ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3238 የላብራቶሪ ምርመራ አንድ መቶ ሰላሳ አንድ (131) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 4663 ደርሷል። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 94 ወንድ እና 37 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ 2 እስከ 80 ዓመት ውስጥ ይገኛል። በዜግነት አንድ መቶ ሰላሳ (130) ሰዎች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንድ ሰው የውጭ ሃገር ዜጋ ነው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 98 ሰዎች ከአዲስ አበባ ፣ 16 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሰዎች ከሶማሊ ክልል፣ 3 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 3 ሰዎች ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ 3 ሰዎች ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል፣ 2 ሰዎች ከጋምቤላ ክልል፣ 1 ሰው ከአማራ ክልል እና 1 ሰው ከትግራይ ክልል ናቸው።
ከጠቅላላው የላብራቶሪ ምርምራ ውስጥ 26 (10 ከጤና ተቋም እና 16 ከማህበረሰብ በተወሰደ ናሙና) ናሙናዎች በአስክሬን ላይ የተደረገ የላብራቶሪ ምርምራ ሲሆን የ80 ዓመት ወንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከማህበረሰብ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ሰባ አምስት (75) ደርሷል፡፡ በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት ሰማንያ አራት (84) ሰዎች (79 ሰዎች ከ አዲስ አበባ፣ 2ሰዎች ከኦሮሚያ፣ 2 ሰዎች ከትግራይ እና 1 ሰው ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1297 ነው።
በሕብረተሰቡ ውስጥ ባለው የቫይረስ ስርጭት ምክንያት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። በመሆኑም እኛ ወይም የምንወደው ሰው ቀጥሎ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ልንሆን እንደሚችል በመገንዘብ ከመቼውም ግዜ በላይ በመጠንቀቅ ስርጭቱን ማቆም እንችላለን። በዚህ ወረርሽኝ አንዳችን ለአንዳችን ዘብ በመቆም የኮሮና ቫይረስ የመከላከያ ዘዴዎችን ለመተግበር አንዳችን ስንዘናጋ ሌላችን ካስታወስን ህይወት ልናተርፍ እንችላለን። በመሆኑም የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን አንዱን ዘዴ ከሌላው ሳናማርጥ በሙሉ መተግበር ይገባናል።
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 219,566 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 3238 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 131 |
በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው | 3,289 |
በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር | 38 |
አዲስ ያገገሙ | 84 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 1,297 |
በዕለቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች | 1 |
በአጠቃላይ በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 75 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 4663 |
በየዕለቱ የሚቀርበው የኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ ምላሽ አሰጣጥን የተመለከተ መግለጫ ከሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በhttp://covid19.et ላይ የሚገኝ የሚሆን ይሆናል።
የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም