ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4457 የላብራቶሪ ምርመራ ስልሳ ሶስት (63) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 4532 ደርሷል። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 42 ወንድ እና 21 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ14 እስከ 76 ዓመት ውስጥ ነው። በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ 31 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 9 ሰዎች ከሶማሊ ክልል፣ 5 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሰዎች ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ 4 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 3 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 3 ሰዎች ከጋምቤላ ክልል፣ 2 ሰዎች ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል፣ 1 ሰው ከትግራይ ክልል እና 1 ሰው ከሐረሪ ክልል ናቸው።
ከጠቅላላው የላብራቶሪ ምርምራ ውስጥ 18 (5 ከጤና ተቋም እና 13 ከማህበረሰብ በተወሰደ ናሙና) ናሙናዎች በአስክሬን ላይ የተደረገ የላብራቶሪ ምርምራ ሲሆን ከአንድ የ75 ዓመት ወንድ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶበታል። ከዚህ በተጨማሪ በለይቶ በህክምና ማዕክል ውስጠ ክትትል ላይ የነበረች የ34 ዓመት ሴት የአዲስ አበባ ነዋሪ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወቷ ያለፈ ሲሆን በጠቅላላ ሁለት ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ህይወታቸው አልፋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ሰባ አራት (74) ደርሷል፡፡ በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
በቅርቡ የዴክሳሜታዞን (Dexamethasone) መድኃኒት ኦክሲጅን ወይም የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ በሚያስፈልጋቸው የኮቪድ-19 ህሙማን ዘንድ ሊከሰት የሚችለውን የሞት አደጋ መቀነስ እንዳስቻለ መገለጹ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር በሀገራችን ኦክሲጅን ወይም የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው የኮቪድ-19 ህሙማን የህክምና ባለሙያዎች በሚያዙት መሰረት ዴክሳሜታዞን እንደ ድንገተኛ ህክምና ጥቅም ላይ እንዲውል ወስኗል ።
ነገር ግን ዴክሳሜታዞን የኮቪድ-19 መድኃኒት ያለሆንና ለመከላከል የማይጠቅም ሲሆን የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ግንዛቤ እንዲወሰድ እና ያልታመሙ ሰዎች ያለህክምና ባለሙያ ትዕዛዝ ከወሰዱት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።ሕብረተሰቡ ያለሀኪም ትዕዛዝ መድኃኒቱን እንዳይወስድ እንዲሁም የፋርማሲ እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም የዴክሳሜታዞን መድኃኒትን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ለደንበኞቻቸው መሸጥ እንደሌለባቸው በአጽንኦት እናሳስባለን፡፡
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት ዘጠና አንድ (91) ሰዎች (67 ከአዲስ አበባ፣ 16 ከሶማሊ ክልል፣ 4 ከአማራ ክልል፣ 2 ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እና 2 ከኦሮሚያ ክልል) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1213 ነው።
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 216328 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 4457 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 63 |
በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው | 3243 |
በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር | 32 |
አዲስ ያገገሙ | 91 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 1213 |
በዕለቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች | 2 |
በአጠቃላይ በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 74 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 4532 |
የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም