ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 5644 የላብራቶሪ ምርመራ ሁለት መቶ ስልሳ ስምንት (268) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3,166 ደርሷል። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 177 ወንድ እና 91 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ 1 እስከ 90 ዓመት ውስጥ ይገኛል። በዜግነት ሁለት መቶ ስልሳ ሰባቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንድ የውጭ ሃገር ዜጋ ነው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሁለት መቶ ሰላሳ ሁለቱ (232) ሰዎች ከአዲስ አበባ ፣ አስራ ሁለት (12) ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ ስምንት (8) ሰዎች ከአማራ ክልል ፣ ስድስት (6) ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ አምስት (5) ሰዎች ከሐረሪ ክልል፣ ሁለት (2) ሰዎች ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል፣ ሁለት (2) ሰዎች ከአፋር ክልል እንዲሁም አንድ (1) ሰው ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ናቸው።
ማስተካከያ፦ በሰኔ 4 ቀን ሪፖርት በተደረገው የዕለታዊ መግለጫ ቫይረሱ በምርመራ እንድተገኘባቸው ከተገለፁት ሰዎች መካከል አስራ ሰባቱ (17) ሰዎች ከዚህ ቀደም ሪፖርት ተደርገው በህክምና ማዕከል ውስጥ ያሉ እና ለክትትል ምርመራ የተደረገላቸው መሆናቸውን ከይቅርታ ጋር እንገልፃለን። በመሆኑም በሰኔ 4 ዕለት ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር አንድ መቶ አርባ ሰባት (147) ናቸው።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ የስምንት ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል። በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ሃምሳ-አምስት (55) ደርሷል፡፡ በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ዝርዝር ሁኔታ እንደሚከለው ቀርቧል፡፡
ተ.ቁ | የመኖሪያ አድራሻ | ጾታ | ዕድሜ | ማብራሪያ |
1 | አዲስ አበባ | ወንድ | 65 | በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበረ |
2 | አዲስ አበባ | ሴት | 34 | በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበረች |
3 | አዲስ አበባ | ወንድ | 45 | በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበረ |
4 | አዲስ አበባ | ሴት | 40 | በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ የነበረች |
5 | አዲስ አበባ | ወንድ | 90 | በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘ |
6 | አዲስ አበባ | ወንድ | – | በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘ |
7 | አዲስ አበባ | ወንድ | 50 | በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘ |
8 | አዲስ አበባ | ሴት | 45 | በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘ |
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት አርባ አራት (44) ሰዎች (28 ከአዲስ አበባ፣ 6 ከአማራ ክልል፣ 4 ከአፋር ክልል፣ 3 ከኦሮሚያ ክልል እና 3 ከሐረሪ ክልል) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 495 ነው።
በሕብረተሰቡ ውስጥ ባለው የቫይረስ ስርጭት ምክንያት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። በመሆኑም እኛ ወይም የምንወደው ሰው ቀጥሎ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ልንሆን እንደሚችል በመገንዘብ ከመቼውም ግዜ በላይ በመጠንቀቅ ስርጭቱን ማቆም እንችላለን። በዚህ ወረርሽኝ አንዳችን ለአንዳችን ዘብ በመቆም የኮሮና ቫይረስ የመከላከያ ዘዴዎችን ለመተግበር አንዳችን ስንዘናጋ ሌላችን ካስታወስን ህይወት ልናተርፍ እንችላለን። በመሆኑም የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን አንዱን ዘዴ ከሌላው ሳናማርጥ በሙሉ መተግበር ይገባናል።
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 176,504 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 5,644 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 268 |
በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው | 2,614 |
በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር | 39 |
አዲስ ያገገሙ | 44 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 495 |
በአጠቃላይ በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 55 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 3,166 |
የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ሰኔ 6 ቀን 2012 ዓ.ም