የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከውጭ የሚመጡ ሰዎችን ለ14 ቀናት በአስገዳጅ ለይቶ መቆያ በማቆየት ምርመራና ክትትል ማድረግ፣ በምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡ ሰዎችን ወደ በሕክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ የህክምና ክትትል ማድረግ እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች በመለየት ምርመራና ክትትል ማድረግ ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው። እነዚህ እርምጃዎች ራሳችንን፣ የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችንና ህብርተሰቡን ከበሸታው ለመከላከል ያስችላል እንዲሁም በወረርሽኙ መስፋፋት ሊፈጠር የሚችለውን የሰው ሕይወት ሕልፈት፣ የስነ-ልቡናዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መቀነስ ይቻላል። ለዚህም የሕብረተሰቡ እንዲሁም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና እገዛ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ከምንጊዜውም በላይ የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ የጠበቀ ጥሪያችንን ማስተላለፍ እንወዳለን።
ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4775 የላብራቶሪ ምርመራ መቶ ሰላሳ ስድስት (136) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2156 ደርሷል፡፡ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 85 ወንድ እና 51 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ 1 እስከ 97 ዓመት ውስጥ ይገኛል። በዜግነት መቶ ሃያ አራት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አስራ ሁለቱ የውጭ ሃገር ዜጎች ናቸው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው አንድ መቶ አስራ አምስት (115) ሰዎች ከአዲስ አበባ ፣ዘጠኝ (9) ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ ሰባት (7) ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ ሁለት (2) ሰዎች ከሐረሪ ክልል፣ ሁለት (2) ሰዎች ከሶማሊ ክልል እንዲሁም አንድ (1) ሰው ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ናቸው።
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት አስራ ሰባት (17) ሰዎች (8 ከአዲስ አበባ፣5 ከአማራ ክልል፣ 2 ከአፋር ክልል እና 2 ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 361 ነው።
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 147,735 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 4775 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 136 |
በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው | 1766 |
በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር | 32 |
አዲስ ያገገሙ | 17 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 361 |
በአጠቃላይ በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 27 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 2,156 |
የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም