ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 5500 የላብራቶሪ ምርመራ አንድ መቶ ሃያ ዘጠኝ (129) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1934 ደርሷል፡፡ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 75 ወንድ እና 54 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ 1 እስከ 90 ዓመት ውስጥ ይገኛል። በዜግነት መቶ ሃያ አራት ሰዎች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የተቀሩት የደቡብ አፍሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ የአሜሪካ፣ የኤርትራ እና የሱዳን ዜጎች ናቸው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው አንድ መቶ አንድ (101) ሰዎች ከአዲስ አበባ ፣ አስር (10) ሰዎች አማራ ክልል፣ ስድስት (6) ሰዎች ከሶማሊ ክልል፣ አምስት (5) ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ አምስት (5) ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ አንድ (1) ሰው ከሐረሪ ክልል እና አንድ (1) ሰው ከጋምቤላ ክልል ናቸው።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ለመቆጣጠር እና የህብረተሰቡን ጤና ለመታደግ መተኪያ የሌለውን ህይወታችውን አጋልጠው በግንባር ቀደምነት ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ ላሉ እና አርአያነት ያለው ተግባር እየፈጸሙ ላሉ የጤና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
የጤና ተቋማት ሰራተኞቻቸው ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሚያስችል ጠንካራ የብክለት መከላከልና መቆጣጠር ስርዓትን መተግበር ግድ ይላቸዋል፡፡ ለዚህም ከመግቢያ በር ጀምሮ የልየታ ስራውን ማጠናከር የሚያስፈልግ ሲሆን የተገልጋዮችና ሰራተኞች እንቅስቃሴ የብክለት/ኢንፌክሽን መከላከልን መሰረት ባደረገና ርቀትን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን የሚያስችል የውስጥ ዲዛይን ማስተካከያ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አስፈላውን የግል መከላከያ ቁሳቁሶች ለሰራተኞች በማቅረብ፣ የእውቀትና ክህሎት ክፍተቶችን በመለየትና በመሙላት ሰራኞቻቸው ለኮሮና ቫይረስ በሽታ እንዳይጋለጡ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ የጤና ሙያተኞችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችም አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት፣ ከህሙማን፣ ከስራ ባልደረቦቻቸው እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ሳይዘናጉ በሁሉም ቦታ፣ጊዜና ሁኔታ ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ የአንድ የ80 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊ የ አዲስ አበባ ነዋሪ ህይወት አልፏል። ሟቿ ወደ ሆስፒታል ለሌላ ህክምና በመጡ በአንድ ሰዓት ወስጥ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። በአስክሬን ምርመራም የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ሃያ (20) ደርሷል፡፡ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት አስራ ዘጠኝ (19) ሰዎች (2 ከትግራይ ክልል፣ 6 ከአፋር ክልል፣ 1 ከሶማሊ ክልል እና 10 ከአዲስ አበባ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 281 ነው።
የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 136,868 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 5500 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 129 |
በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው | 1631 |
በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር | 27 |
አዲስ ያገገሙ | 19 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 281 |
በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 20 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 1934 |
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ግንቦት 29 ቀን 2012 ዓ.ም