ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4120 የላብራቶሪ ምርመራ አንድ መቶ አርባ ሁለት (142) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1,486 ደርሷል፡፡ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 84 ወንድ እና 57 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ7 እስከ 78 ዓመት ውስጥ ይገኛል። በዜግነት 140 ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ሁለቱ የፖርቹጋል እና የጅቡቲ ዜጎች ናቸው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው አንድ መቶ ሃያ ስድስት (126) ሰዎች ከአዲስ አበባ ፣ ሁለት (2) ሰዎች ከአፋር ክልል፣ ሰባት (7) ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ ስድስት (6) ሰዎች አማራ ክልል እና አንድ (1) ሰው ከሶማሊ ክልል ናቸው።
የላቦራቶሪ ውጤቶች እንደሚያሳዩት በሕብረተሰቡ ውስጥ ባለው የቫይረስ ስርጭት ምክንያት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። ለዚህም ማሳያ የመጀመሪያው ሰው በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ300 መቶኛ በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የታከሚዎች ቁጥር በመጨመሩ እንደ ሚሊኒየም አዳራሽ አይነት የለይቶ ማከሚያዎች ታካሚዎችን እንዲቀበሉ ማድረግ ተጀምሯል፡፡
ስለዚህ ሕብረተሰቡ የእጅ ንጽኅናውን በመጠበቅ፣ በቤት በመቆየት እንዲሁም ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ባለመገኘት፣ ከማንኛውም ሰው በ 2ሜትር አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ራሱንና የሚወዳቸውን ሁሉ ከቫይረሱ እንዲጠብቅ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማሳሰብ ይወዳሉ፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ የሶስት ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል። የመጀመርያዋ የ71 ዓመት ሴት የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ሁለተኛ የ46 ዓመት ወንድ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ እና ሶስተኛ የ40 ዓመት ወንድ የደቡብ ክልል ነዋሪ ሲሆኑ የመጀመሪያዋ ግለሰብ በሆስፒታል ውስጥ ህክምና ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ሁለቱ ህይወታቸው አልፎ ለአስክሬን ምርመራ በሆስፒታል በተደረገ ምርምራ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር አስራ ሰባት (17) ደርሷል፡፡ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት አስራ አምስት ሰዎች (ዘጠኝ ከሶማሊ ክልል እና ስድስት አዲስ አበባ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 246 ነው።
የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 120,429 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 4,120 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 142 |
በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው | 1,219 |
በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር | 6 |
አዲስ ያገገሙ | 15 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 246 |
በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 17 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 1486 |
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም