Categories
Amharic

የኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ የተዘጋጀ መግለጫ ግንቦት-12

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3460 የላብራቶሪ ምርመራ ሃያ አራት (24) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ሶስት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ (389) ደርሷል፡፡ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 18 ወንድ እና 6 ሴት ናቸው፡፡ በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ከ 4 እስከ 57 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ዘጠኝ (9) ሰዎች ከአዲስ አበባ (አምስት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እና አራት ሰዎች የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው)፣ ሰባት (7) ሰዎች ከትግራይ ክልል (አራት የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው እና ሶስት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ከነዚህም ውስጥ አንድ መቀሌ ለይቶ ማቆያ ያለ ሲሆን ስድስቱ ማይካድራ ለይቶ ማቆያ ያሉ ናቸው) እንዲሁም ስምንት (8) ሰዎች ከአማራ ክልል (የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው እና መተማ ለይቶ ማቆያ ያሉ)  ናቸው፡፡

የዕለቱ ታማሚዎች የተጋላጭነት ሁኔታ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የተጋላጭነት ሁኔታቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር
የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው12
በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው8
የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው4
 ድምር24

በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት ሁለት (2) ሰዎች ከአማራ ክልል ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር አንድ መቶ ሃያ ሁለት (122) ነው።

የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡

በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ

አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ65,760
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ3460
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ24
በአጠቃላይ በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ከህክምና ውስጥ ያሉ260
በፅኑ ህክምና ላይ ያሉ0
አዲስ ያገገሙ2
በአጠቃላይ ያገገሙ122
በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ5
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ2
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር389

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ  ሥርጭት መጨመርን ከግንዛቤ በማስገባት ሕብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ እንዲተገብር ያሳስባሉ። በበሽታው መያዛችን ዕለት-ተዕለት በምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚወሰን መሆኑን በማስታወስ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ አራቱን የ’’መ’’ ህጎች ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንድንከላከል በጥብቅ እናሳስባለን።   

  • መራራቅ፡ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣
  • መታጠብ፡ እጅን በተደጋጋሚ በውሃና በሳሙና መታጠብ፣
  • መቆየት፡ አስገድጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየት እንዲሁም
  • መሸፈን፡ ከቤታችን ወጥተን ስንቀሳቀስ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) መጠቀም

በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡

ዶ/ር ሊያ ታደሰ

የጤና ሚኒስትር

ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *