ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 1775 የላብራቶሪ ምርመራ ሰላሳ አምስት (35) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ሶስት መቶ ሃምሳ ሁለት (352) ደርሷል፡፡ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 17 ወንድ እና 18 ሴት ናቸው፡፡ በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ከ15 እስከ 80 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሃያ ዘጠኝ (29) ሰዎች ከአዲስ አበባ (አንድ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያለው የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ ፣ 23 በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ 5 ሰዎች የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው)፣ አንድ (1) ሰው ከኦሮሚያ ክልል (የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ)፣ አራት (4) ሰዎች ከሶማሊ ክልል (ጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ) እንዲሁም አንድ (1) ሰው ከአማራ ክልል (ሰሜን ሸዋ ዞን፤ አጣየ ከተማ ለይቶ ማቆያ) ነው፡፡
ሚያዚያ 27 በተሰጠው መግለጫ በኮቪድ-19 ምክንያት የ75 ዓመት ሴት ህይወታቸው ማለፉን መግለፃችን ይታወሳል። በመሆኑም ከግለሰቧ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው 25 ሰዎች ተለይተው ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው በተደረገ የላብርቶሪ ምርመራ አምስት ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጦ በግንቦት 1 ቀን በተሰጠው መግለጫ የተካተቱ ነበሩ። በዛሬው ዕለት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ውስጥ 22 ሰዎች በግንቦት 1 ቀን ከተገለጹት አምስት ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው እና ክትትል ላይ ከነበሩ 94 ግለሰቦች ውስጥ ናቸው።
የዕለቱ ታማሚዎች የተጋላጭነት ሁኔታ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የተጋላጭነት ሁኔታ | ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር |
የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው | 6 |
በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው | 24 |
የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው | 5 |
ድምር | 35 |
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት ሶስት (3) ሰዎች ከአዲስ አበባ ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር አንድ መቶ አስራ ስድስት (116) ነው።
በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ
አጠቃላይ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 59,029 |
በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተከናወነ የላብራቶሪ ምርመራ | 1775 |
በዛሬው ዕለት በበሸታ መያዛቸው በላብራቶሪ የተረጋገጠ | 35 |
በአጠቃላይ በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ከህክምና ውስጥ ያሉ | 229 |
በፅኑ ህክምና ላይ ያሉ | 0 |
አዲስ ያገገሙ | 3 |
በአጠቃላይ ያገገሙ | 116 |
በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ | 5 |
ወደ ሀገራቸው የተመለሱ | 2 |
እስከ አሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር | 352 |
የላብራቶሪ ምርመራ ናሙናዎች ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መጨመርን ከግንዛቤ በማስገባት ሕብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ እንዲተገብር ያሳስባሉ። በበሽታው መያዛችን ዕለት-ተዕለት በምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚወሰን መሆኑን በማስታወስ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ አራቱን የ’’መ’’ ህጎች ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንድንከላከል በጥብቅ እናሳስባለን።
- መራራቅ፡ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣
- መታጠብ፡ እጅን በተደጋጋሚ በውሃና በሳሙና መታጠብ፣
- መቆየት፡ አስገድጅ ካልሆነ ቤት ውስጥ መቆየት እንዲሁም
- መሸፈን፡ ከቤታችን ወጥተን ስንቀሳቀስ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) መጠቀም
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የጤና ሚኒስትር
ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም