Categories
Amharic

የህዝብ ግንኙነትና የተግባቦት ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እያደረጉ ያለውን ጥረት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ ቦታዎች ለኮሮና ቫይረስ በሽታ ስርጭት ምቹ እንዳይሆኑና ሰራተኞች በኮሮና ቫይረስ በሽታ እንዳይያዙ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር በፌዴራል ደረጃ ለሚገኙ የህዝብ ግንኙነትና ተግባቦት አመራሮችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡
በስልጠናው የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ እንደገለጹት ሰራተኞች የተሰጣቸውን የስራ ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡና እንደሃገር የተያዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕቅዶችን ማሳካት የሚቻለው መጀመሪያ የሰራተኞቻችንና የዜጎቻችን ጤና መጠበቅ ስንችል ብቻ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የህዝብ ግንኙነትና የተግባቦት ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ተገኔ አክለውም በአሁኑ ወቅት ከፊታችን የተደቀነብንን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከልና በሰራተኞች ሊኖር የሚችለውን ስርጭት መግታት የሚቻለው የበሽታውን መተላለፊያና መከላከያ መንገዶችን ሰራተኞች ጠንቅቀው እንዲያውቁ ማድረግና በትግበራው ሂደትም የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ ስንችል ስለሆነ ወረርሽኙን ለመከላከል እያደረጋችሁት ያለውን ጥረት የበለጠ አጠናክራችሁ ልትቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ አስራ ስድስት ሰልጣኞች የተሳተፉ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል በየመስሪያ ቤቶቻቸው ያላቸውን ተሞክሮ እና በትግበራ ሂደት የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች አቅርበው ውይይት አድርገውባቸዋል፡፡ በሽታው እንደተከሰተ ሰሞን የንጽህና መጠበቂያ ቦታዎችን በማዘጋጀት፣ ሰራተኞች ወደስራ ቦታ ሲገቡ እጃቸውን በሳሙና እና በውሃ ታጥበው እንዲገቡ በማድረግ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አድርገው እንዲገቡ በማድረግና ሙቀታቸውን ተለክተው እንዲገቡ ሲደረግ የነበረው ተነሳሽነት በጥንካሬ የተነሱ ናቸው፡፡ የበሽታው ስርጭት እየጨመረ ሲመጣ ግን ጥንቃቄን የበለጠ ከማጠናከር ይልቅ መዘናጋትና ቸልተኝነት በስፋት እየተስተዋለ መምጣቱ፣ ርቀትን ከመጠበቅ ይልቅ በቡድን ተጠጋግቶ ሻይ ቡና ማለት፣ ማስክን በአግባቡ አለማድረግ፣ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ቀስ በቀስ መዳከም፣ በመሳሪያው ብልሽት ምክንያት ሰራተኞች የሙቀት ልኬት ሳይደረግላቸው እንዲገቡ የሚያደርጉ ተቋማት መኖራቸውና በአንዳንድ ተቋማት የሙቀት መለኪያ መሳሪያ ጭራሽ አለመኖሩ ደግሞ በክፍተት መልክ የቀረቡ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰራተኞች እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡
የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ወደ ተቋማቸው ሲመለሱ በተቋማቸው የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል የሚሰሯቸውን ስራዎች የሚከታተሉበት ቅጽ ተዘጋጅቶ የቀረበላቸው ሲሆን በቀጣይ የስራ ቦታዎችን ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ምቹ እንዳይሆኑ በማድረግ ሰራተኞቻቸውን ከበሽታው ለመታደግ ትኩረት ሰጥትን እንሰራለን ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *