የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፍጥነት በአለም አቀፍ ደረጃ ብሎም በሀገራችን እየተዛመተ ይገኛል፡፡ በእኛ ሀገር የስርጭት ሁኔታ ስንመለከት በትላንትናው እለት ብቻ ናሙና ከሰጡ 6,089 ግለሰቦች መካከል 977 ያህሉ በኮቪድ-19 ተይዘዋል፡፡
ይህም ማለት ናሙና ከሰጡት 100 ግለሰቦች 16ቱ(16%) በቫይረሱ እንደተያዙ ያሳያል፡፡ይህ ቁጥር በባለፈው ሳምንት ( የካቲት 14) ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ሲሆን በትላንትናው እለትም ለሁለተኛ ጊዜ ተመዝበግዋል:: ይህ የሚያሳየው የኮቪድ-19 ስርጭት በሀገራችን ምን ያህል አስጊ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ነው፡፡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎች ጭምር ነው፡፡ለማሳያነት በትላንትናው እለት የሶስት ክልሎችን ብናይ በአዲስ አበባ ናሙና ከሰጡ 4614 ግለሰቦች መካከል 854 ግለሰቦች ወይም 19 በመቶ (19%) የተያዘ ሲሆን ፤ በኦሮሚያ ክልል ናሙና ከሰጡ 286 ግለሰቦች 70 የሚሆኑት ወይም 24 በመቶ (24%) መያዛቸውን ያሳያል፤እንዲሁም በሲዳማ ክልል ናሙና ከሰጡ 85 ግለሰቦች 21 ግለሰቦች ወይም 25 በመቶ (25%) ቫይረሱ እንዳለባቸው ያሳያል፡፡ ይህ አሀዝ የሚያሳየው የ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልሎችም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን ነው፡፡
ወደ ፅኑ ህሙማን ህክምና ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥርም እየጨመረ ይገኛል፡፡እስከ ትላንትናው እለት ብቻ 386 ግለሰቦች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የገቡ ሲሆን፤ ወደ ህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 70 ግለሰቦች(70%) የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በትላንትናው ዕለት ብቻ ፅኑ ህክምና የሚያስፈልጋቸው 61 ቫይረሱ የተገኝባቸው ግለሰቦች ተመዝግብዋል፤ ይህ ቁጥር ከነሐሴ 2012 በሁላ የመጀመሪያ ከፍተኛ ቁጥር ነው፡፡
የሞት ምጣኔውንም ስናይ ደግሞ እስከ ትላንትናው እለት ብቻ 2,316 ግለሰቦች ህይወት አልፏል ይህ ማለት በዚህ ሳምንት ብቻ በአማካኝ በቀን 11 ግለሰቦች ህይወታቸውን በኮቪድ -19 እያጡ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ፤ ቤተሰብ፤ ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የሐይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የጤና ባለሙያዎች፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከከልና ለመቆጣጠር ተግባር ላይ በባለቤትነት እና በኃላፊነት ስሜት አጠናክረው እንዲሠሩ እናሳስባለን፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
#እንድናገለግልዎማስክዎንያድርጉ
#COVID19Ethiopia
#NOMASKNOSERIVCE