በአለም ዙሪያ በየደቂቃው በኮቪድ-19 የሚያዙ እና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን 2‚128‚036 የኮቪድ -19 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 158‚053 ግለሰቦች ላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ፤ በትላንትናው ዕለት 14 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን እስካሁን 2‚354 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት ከተመረመሩት 6‚759 ውስጥ 1‚006 ግለሰቦች ቫይረሱ ሲኖርባቸው፤ ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች 15 ግለሰቦች ወይም (15%) መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህን ያህል ግለሰቦች በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዙት በማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ (COMBAT) ወቅት ነው፡፡ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ፤ የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ (COMBAT) ከመጀመሩ በፊት እንዲሁም በኃላ በቀን የዚህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቦ አያውቅም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ፤ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እንዲሁም በኮቪድ -19 ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ እያንዳንዱ ግለሰብ፤ ቤተሰብ፤ ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የሐይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የጤና ባለሙያዎች፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግ ፣ የእጃቸውን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እዲያደርጉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሳስባል፡፡
#እንድናገለግልዎማስክዎንያድርጉ
#COVID19Ethiopia #NOMASKNOSERIVCE