ባሳለፍነው ሳምንት ከየካቲት 22 -28 /2013 ባለው መረጃ መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተያዙ ግለሰቦች በ
2% ያህል መጨመር አሳይቷል።በአፍሪካም በዚሁ ሳምንት በ10% በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙ ግለሰቦች ጭማሪ አሳይቷል ፤
በኢትዮጵያ ቫይረሱ የመሰራጨት አቅሙን ጨምሮ አስጊ በሆነ ደረጃ በ12.80% በኮቪድ-19 የመያዝ ምጣኔ ጨምሯል፡፡
በትላንትናው እለት መጋቢት 01/2013 በኢትዮጵያ 7,819 ግለሰቦች የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም
ውስጥ 1,543 ግለሰቦች የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች 20 ያህሉ ወይም 20%
የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበው በነሐሴ/2012 በማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና
ምርመራ ዘመቻ (COMBAT) ወቅት ብቻ ነው፡፡ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ
ይገኛል፡፡ እስከ ትላንትናው እለት ብቻ 438 ግለሰቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ እለት
ጀምሮ ይሄ ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የ2‚446 ግለሰቦች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በትላንትናው እለት
ብቻ 15 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የኮቪድ-19 ቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ የሚገኘው በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ማሳያነት አዲስ አበባን ጨምሮ በትላንትናው
ዕለት ብቻ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡ ክልሎችን ብናይ በአዲስ አበባ 6,392 ግለሰቦች ናሙና የሰጡ ሲሆን 1,269 ግለሰቦች ወይም
20% ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ፤በሲዳማ 91 ግለሰቦች ናሙና የሰጡ ሲሆን 35 ግለሰቦች ወይም 38% ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፤
በድሬደዋ 48 ግለሰቦች ናሙና የሰጡ ሲሆን 16 ግለሰቦች ወይም 33% በቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ፤ በኦሮሚያ ክልል 511 ግለሰቦች
ናሙና የሰጡ ሲሆን 149 ግለሰቦች ወይም 29% ያህሉ የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል ፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ 43 ግለሰቦች ናሙና
የሰጡ ሲሆን 11 ግለሰቦች ወይም 25% ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህ መረጃ የሚያሳየው የኮቪድ-19 ቫይረስ ስርጭት በሁሉም
የሀገሪቱ ክፍል በፍጥነት እና በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተዛመተ እንደሚገኝ ነው።
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኝ ግለሰብ ፤ ቤተሰብ ፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፤ የሐይማኖት ተቋማት ፣
ሲቪክ ማህበራት ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግ ፣
የእጃቸውን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች በጋራ እንድንከላከል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና
ኢንስቲትዩት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
መዘናጋት እስከመቼ እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ