Categories
Amharic

በቤት ውስጥ ራስን ለይቶ በማቆየት የኮሮና ቫይረስ በሽታን መከላከል እንደሚቻል ተገለጸ

በቤት ውስጥ ራስን ለይቶ በማቆየት የኮሮና ቫይረስ በሽታን መከላከል እንደሚቻል ተገለጸ
እራስን በቤት ውስጥ ለይቶ በማቆየት ተገቢውን የመከላከያ ዘዴዎችን በመተግበርና ጥንቃቄዎችን በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን መከላከል እንደሚቻል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል ገለጸ፡፡
በማዕከሉ የመግቢያና የመውጫ፣ የለይቶ ማቆያና የልየታ ክፍል ሃላፊ አቶ መሃመድ ናስር እንደገለጹት ከወጪ ሃገር ለሚመጡ ተጓዦች ናሙናው ከተወሰደ ከ5 ቀናት ያልበለጠ የላቦራቶሪ የምርመራ ውጤት (RT-PCR) ይዘው ለመጡና ውጤቱም ከቫይረሱ ነጻ ከሆነ የሙቀት እና የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክቶች ልየታ ተደርጎላቸዉ ናሙና ከተወሰደ በኋላ ሙሉ አድራሻቸውን በመመዝገብ እና የስምምነት ቅፅ እንዲሞሉ በማድረግ እራሳቸውን በቤታቸው ውስጥ ለይተው ለ14 ቀናት በተመደቡላቸው የጤና ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገላቸው መቆየት እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ በሽታ የላቦራቶሪ የምርመራ ውጤት (RT-PCR) ሳይዙ ወደ ሃገር የሚመጡ መንገደኞች ደግሞ 7 ቀናት በለይቶ ማቆያ ሆቴል ክትትል ተደርጎላቸው ኮሮና ቫይረስ በሽታ ናሙና ተውስዶላቸው ውጤታቸው ኒጋቲቪ የሆነ ቀሪውን 7 ቀናት በወጣው መመሪያ መስፈርት መሰረት እራሳቸውን በቤታቸው ለይተው ማቆየት እንደሚችሉ እና ውጤታቸው ፖዘቲቭ የሆነ ደግሞ በመመሪያው መሰረት የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጣቸው የክፍሉ ሃላፊው አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የውጪ ሀገር መንገደኞች በአዋጅ መመሪያ መስፈርት መሰረት እራሳቸውን በቤታቸው ለይተው በማቆየት ክትትል እንዲያድርጉ ያስፍለገበት ዋና ምክንያትን አቶ መሃመድ ናስር ሲያስረዱ እንደተናገሩት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር ያለባቸዉን ሰዎች ትኩረት አድርጎ ለመስራት እንዲቻል የተዘረጋ የክትትል ስርዓት ነው ብለዋል፡፡
የአዲሱ የጊዜያዊ አዋጅ መመሪያ ከተጀመረበት ከሰኔ 14/2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከዉጭ ሀገር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የገቡ መንገደኞች ብዛት 24,359 እንደሆኑ፤ የኮቪድ-19 የላቦራቶሪ የምርመራ ውጤት (RT-PCR ) ነጌቲቭ የሆነ ከ5 ቀናት ያልበለጠ ውጤት ይዘው የመጡ መንገደኞች ደግሞ 16,435 የደረሱ ሲሆን የሙቀት እና የኮቪድ-19 ምልክቶች ልየታ በማድረግ ናሙና ከተወሰደላቸው በኋላ ሙሉ አድራሻቸው ተመዝግቦ የስምምነት ቅፅ እንዲሞሉ በማድረግ በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው ለ14 ቀናት እንዲቆዩ መደረጉን አቶ መሃመድ ተናግረዋል፡፡
አቶ መሃመድ አክለውም የላቦራቶሪ የምርመራ ውጤት (RT-PCR) ያልያዙ ወደ ሃገራቸችን የመጡ 8,961 የሚሆኑ መንገደኞች 7 ቀናት በለይቶ ማቆያ ሆቴል እና ማዕከል እንዲቆዩ ተደርገው ቀሪውን ጊዜ በቤታቸው እራሳቸውን ለይተው በማቆየት ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንና የጤና እክል እና ታያያዥ ችግሮች ያለባቸውን በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ሆቴል ወይም ማዕከል ወስጥ ከሚሰጠው የጤና ክትትል ተጨማሪ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸውና በማቆያው መቆየታቸው ለጤናቸው ተጨማሪ ጫና ይፈጥርባቸዋል ተብሎ የታመነባቸው 207 የሚሆኑ መንገደኞች ደግሞ መረጃ አቅርበው በባለሙያ እንዲረጋገጥ በማድረግ በጤና ተቋማት ክትትል እንዲያደርጉ ስለመደረጉም ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *