በሕብረተሰቡ ዘንድ እየተስተዋለ በሚገኘው መዘናጋት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ክበርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበሽታው ህይወታቸውን የሚያጡ ግለሰቦች ቁጥር መጨመሩንም ገልፀዋል።
የፅኑ ሕሙማን ቁጥር ከአቅም በላይ መሆኑ እና ቤት ውስጥ ህክምናቸውን የሚከታተሉ ሰዎች ህመሙ እስኪባባስ ድረስ ቤት ውስጥ ማሳለፋቸው ለጽኑ ህሙማን ቁጥር መጨመር አንድ ምክንያት እንደሆነ ክብርት ሚኒስትሯ፤ጠቅሰው በቤት ውስጥ ህክምና እየተጥናከረ መሆኑ ጥሩ ጎን ቢሆንም ነገር ግን እስኪባባስ መቆየትና ኦክስጅን በቤት ውስጥ እየተሰጠ መሆኑም ማወቅ እንደተቻለ አስታውቀዋል ። ይህም ሊቆም የሚገባውና ህመሙ የመባባስ ምልክት ሲታይ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባ ተናግረዋል ።
ይህ ሁሉ አስፈሪ ሁኔታ በዙሪያችን እያለም እንደ ማህበረሰብ የአደጋውን ያህል እየተጠነቀቅን እንዳልሆነ ነው ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሠ የተናገሩት፡፡ የማስክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል፣ የሰርግና የሃዘን ስነ-ስርዓቶች፣ የአደባባይ ትርኢቶች፣ የተጨናነቁ ምግብ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ የሙዚቃና የስፖርት ክንውኖች እንዲሁም የማህበራዊ ስነ-ስርዓቶች በብዛት ያለጥንቃቄ እየተከናወኑ መሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ እንዳደረገው ክብርት ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ችግር ለመውጣትም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሠ ጠቅሰው በሁሉም ተቋማት ያሉ ሰራተኞችና ተገልጋዮች ማስክ እንዲያደርጉ ማበረታታትና ማስገደድ እንደሚገባ፣ የህግ አስከባሪው አካልም ያለማስክ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ማስክ እንዲጠቀሙ የመምከርና የማስገደድ ስራቸውን እንዲያጠናክሩ፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ማለትም የትራንስፖርት፣ የእምነት ተቋማት፣ መዝናኛ ቦታዎች እና እድሮች ሃላፊነታቸውን በተሟላና በተገቢ ጥንቃቄ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡