ምልክቶች

በጣም የተለመዱት COVID-19 ምልክቶች ትኩሳት ፣ ሳል እና የትንፋሽ እጥረት ናቸው ።

የበሽታው ምልክት እስከሚታይ ያለው ጊዜ

እንደ መርስ ኮቭ እና ሳርስ ኮቭ ባሉ የኮሮና ቫይረስ አይነቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት  ከሆነ ቫይረሱ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ የበሽታው ምልክቶች እስከሚታዩ ከ 2 እስከ 14 ቀናት ሊቆይ ይችላል፡፡ የሕመምተኛው ዕድሜ እና የበሽታ መከላከል አቅም በሽታው የሚታይባቸውን ጊዜ እና የህመም የጊዜ ቆይታ ልዩነት ይፈጥራል፡፡

ምልክቶች

በአብዛኛው በኮቪድ -19 የተያዙ ታማሚዎች ትኩሳት፣ሳል እና የትንፋሽ እጥረት ምልክቶች ይኖሯቸዋል፡፡ በተጨማሪም ህመምተኞች ራስ ምታት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ሳል፣ የጡንቻ ህመም፣ ድካም፣ የጉሮሮ እና የደረት ህመም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አነስተኛ መጠን ያላቸው ህመምተኞች ከአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና ተቅማጥ ሊኖራቸው ይችላል።

ከባድ ህመሞች

የኮቪድ-19 በሽታ ከተጠቀሱት ቀላል የመተንፈሻ ምልክቶች በተጨማሪ ከባድ የሳንባ ምች፣ የልብ ህመም፣ የጉበት እና የኩላሊት በሽታ እና ስራ ማቆም ሊያስከትል ይችላል፡፡እንዲህ ያሉ ችግሮች ያጋጠማቸው ሕመምተኞች የትንፋሽ መቆራረጥ፣ የአየር ማጠር፣ የደረት ህመም ወይም ደረት ላይ የሚኖር የግፊት ስሜት፣ ራስን መሳት እና መንቃት አለመቻል፣ እንዲሁም በኦክስጅን እጥረት ምክንያት የከንፈሮችን ወይም የፊት ቀለም መቀየር  ሊያሳዩ  ይችላሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ህመምተኞች መለስተኛ / ከባድ ያልሆነ የሳንባ ምች ምልክቶች ወይም  ምንም ዓይነት ህመም ላያሳዩ ይችላሉ፡፡ ከሕመምተኞቹ 14 በመቶ የሚሆኑት እንደ በደም ውስጥ ዝቅተኛ የኦክስጂን  መጠን እና ከባድ የሳንባ ምች ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ከታካሚዎች 5 በመቶ የሚሆኑት የመተንፈሻ አካል እርዳታ የሚጠይቁ ሲሆን ከሳንባ ውጪ ያሉ የአካል ክፍሎች ድክመት ይታይባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን በሽታው የሚያስከትለውን የሞት መጠን ለመደምደም ገና ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ባለው መረጃ ወደ 3 እስከ 5  ከመቶ ገደማ ህይወታቸው ያልፋል፡፡

ኮቪድ-19 አለብኝ ብለው ሲያስቡ ምን ማድረግ አለብዎት?

 • የኮቪድ-19 ምልክቶች ካለብዎ

  • እራስዎን ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ወይም ጓደኞች ያርቁ
  • በሚያስነጥሱበት ወይም በሚያስልዎት ጊዜ አፍዎን እና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም በታጠፈ ክንድዎ ይሸፍኑ
  • አፍንጫዎን እና አፍዎን በጭምብል ይሸፍኑ
  • የተጠቀሙበትን ሶፍት በአግባቡ ክዳን ባለው ቁሻሻ መጣያ ይጣሉ
  • በሐኪም ሳይታዘዙ ማንኛውንም መድሃኒት አይወስዱ
  • የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት ወደ 8335፣952 ወይም አቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም ይደውሉ

ኮቪድ-19ን ከሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እንዴት መለየት ይቻላል?

ሁሉም የጉንፋን ምልክቶች በኮቪድ-19 ምክንያት አይመጡም። አብዛኛዎቹ የኮቪድ-19 ምልክቶች እንደፍሉ፣ ጉንፋን እና አለርጂ ያሉ ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህመም ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ፍሉ በኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ምክንያት የሚመጣ በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ የሆነ የመተንፈሻ አካል በሽታ ነው። ፍሉ እና የተለመደው ጉንፋን ሁለቱም የመተንፈሻ አካላት በሽታ ሲሆኑ የሚመጡት በተለያዩ አይነት ቫይረሶች ነው። ፍሉ የሚያስከትለው የጤና እክሎችን ከተለመደው ጉንፋን አንጻር ከፍተኛ ነው፡፡

ለከባድ ህመም ስጋት ምክንያቶች

በአሁኑ ጊዜ ባለው መረጃ እና የህክምና እውቀት ላይ በመመርኮዝ፣ በዕድሜ የገፉ አዋቂዎች እና በማንኛውም ዕድሜ ላይ ያሉ ከባድ የጤና እክሎች ያለባቸው የማህበረሰብ አባላት ለከባድ ኮቪድ-19 ህመም ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ሲጋራ ማጨስ እና የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ ለበሽታው ከባድ ህመም  አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ዕድሜ – ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ የማህበረሰባችን አባላት ለከባድ ህመም ብሎም ለሞት ተጋላጭ ናቸው።

ጾታ – በጾታ አኳያ እስከአሁን ባለው መረጃ መሰረት ወንዶች በበሽታው ከተያዙትም ሆነ በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ካለፉት ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ።

ሲጋራ ማጨስ – ሲጋራ በሚጨስበት ጊዜ ጣቶች ከአፍ ጋር የሚኖራቸው ንክኪ እንዲሁም ሺሻ በሚጨስበት ወቅት የሚኖር መጋራት በአጫሾች ዘንድ የሚኖረውን የኮቪድ-19 ስርጭት ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ሲጋራ ማጨስ የበሽታውን ስርጭት ከመጨመር በተጨማሪ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች የሳንባ አቅም ስለሚዳከም ለከባድ ህመም የመጋለጣቸው መጠን ይጨምራል፡፡

እንደ ሳንባ፣ የልብ በሽታ፣ የስኳር በሽታ እና የሕመምተኞቹን የመቋቋም አቅም የሚገድቡ በሽታዎች መኖር ከፍ ካለ የሞት መጠን ጋር ይዛመዳል፡፡

አግኙን

 • የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
 • ስዋዚላንድ መንገድ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
 • ስልክ: 0118276796
 • ኢሜል: ephieoc@gmail.com
 • ፖስታ፡ 1242

© 2012, የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ሙሉ መብት የተጠበቀ