Categories
Amharic

መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል

ከቀን ወደ ቀን በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመያዝ ምጣኔ ፤ ህይወታቸውን የሚያጡ እና የፅኑ ህክምና አገለግሎት የሚፈልጉ ታካሚዎች ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። በትላንትናው ዕለት 30 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ቫይረስ ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህ ቁጥር ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያው ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።
በመጋቢት 03 – 04/2013 ፤ በሁለት ቀን ብቻ 57 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በአጠቃላይ 2,540 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ህይወታቸውን አጥተዋል። ከነዚህም ውስጥ 74% የሚሆኑት ከህክምና ማዕከላት ሲሆን 24% ከአስክሬን ላይ ናሙና ወስደን በምንመረምርበት ወቅት የነበረ ነው። በተጨማሪም 1% ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የቤት
ውስጥ ውሸባ እና እንክብካቤ ወቅት ተገቢውን የህክምና ባለሙያ ምክር ባለመተግበር ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች ቁጥር ነው። እስካሁን ከፍተኛ የሞት ቁጥር ያስመዘገቡ ክልሎችን ስንመለከት :-
*አዲስ አበባ ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ 1,852 ግለሰቦች ወይም 73%
*በኦሮሚያ ክልል 256 ግለሰቦች ወይም 10%
*በአማራ ክልል 105 ግለሰቦች ወይም 4%
*በሲዳማ ክልል 75 ግለሰቦች ወይም 3% ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በኮቪድ-19 በትላንትናው ዕለት ለ 7,654 ግለሰቦች ናሙና የሰጡ ሲሆን 1,483 ግለሰቦች የኮቪድ-19 ቫይረስ
ተገኝቶባቸዋል ይህ ማለት ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች 19 ያህሉ ወይም 19% ኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።
በዚሁ ዕለት አዲስ አበባን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡ ክልሎችን ብናይ :-
*በአዲስ አበባ 5,765 ግለሰቦች ናሙና ሰጥተው 1,210 ግለሰቦች ወይም 21%
*በሲዳማ 154 ግለሰቦች ናሙና ሰጥተው 60 ግለሰቦች ወይም 39%
*በኦሮሚያ 622 ግለሰቦች ናሙና ሰጥተው 123 ግለሰቦች ወይም 20% ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
የኮቪድ-19 ቫይረስ በየትኛውም ቦታ ፤ በማንኛውም የዕድሜ ክልል እና ፆታ ሳይመርጥ የሚይዝ እና ህይወት የሚያሳጣ
ስለሆነ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
የህክምና ማዕከላትም መስራት ከሚችሉት አቅም በላይ እየሆነ ስለመጣ ፤ አርቴፊሻል የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ
እና የኦክስጅን እጥረት እያጋጠመ ስለሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠንቀቅ የሚያስፈልግ በመሆኑ እና በአጠቃላይ
በወረርሽኙ የስርጭት ደረጃ መሰባሰቦችን እና አስገዳጅ ያልሆኑ (non-essential) እንቅስቃሴዎችን መገደብ የሚያስገድድ
ወቅት ላይ እንገኛለን። ስለሆነም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኝ ግለሰብ ፤ ቤተሰብ ፤ መንግስታዊና መንግስታዊ
ያልሆኑ ድርጅቶች ፤ የሐይማኖት ተቋማት ፣ ሲቪክ ማህበራት ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤
መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግ ፣ የእጃቸውን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ
አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንድንከላከል የኢትዮጵያ
የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሁንም በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *