ኮቪድ-19 አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በሀገራችን ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ይገኛል፤ በቫይረሱ የሚያዙ ፤ ህይወታቸውን እያጡ ያሉ ፤ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል እየገቡ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር እያሻቀበ ነው።
በትላንትናው እለት 6,282 ግለሰቦች የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 1,161 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ቫይረስ ተይዘዋል።ይህም ማለት ናሙና ከሰጡ100 ግለሰቦች 18 ወይም (18%) ግለሰቦች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ያሳያል ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ አለመተግበራችን ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል።በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተይዘው ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥርም እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፤እስከ ትላንትናው እለት ብቻ 398 ግለሰቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፤ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ እለት ጀምሮ ይሄ ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ወደ ኮቪድ- 19 የህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 69 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ በዛሬው እለት በደረሰን መረጃ ብቻ 19 ያህል ግለሰቦች ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
አሁንም ልብ ይበሉ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ፤ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እንዲሁም በኮቪድ -19 ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ስለመጣ እያንዳንዱ ግለሰብ ፤ ቤተሰብ ፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፤ የሐይማኖት ተቋማት ፣ ሲቪክ ማህበራት ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፤ የጤና ባለሙያዎች ፤ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግ ፣ የእጃቸውን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር እራስዎንም እንዲሁም ወገኖውን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲጠብቁ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፅንኦት ያሳስባል፡፡