ኮቪድ-19 ምንድን ነው?
የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) ሳርስ-ኮቭ 2 (SARS-COV-2) በተሰኘ እና ከዚህ ቀደም ተከስቶ በማያቅ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የሚመጣ የመተንፈስ ችግር የሚያስከትል ተላላፊ በሽታ ነው። ሳርስ ኮቭ -2 በመባል የሚታወቀው ይህ ቫይረስ የ ኮሮና ቫይረስ ዝርያ ቤተሰብ አንዱ ሲሆንከ 80 እስከ120 ናኖ ሜትር (10-9) የሚለካ በአይን የማይታይ ቫይረስ ነው፡፡
ይህ ቫይረስ ከሌሊት ወፍ ከሚገኘው ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ጋር ካለው የ96 በመቶ ቀረቤታ አንፃር ቫይረሱ ከሌሊት ወፍ የተገኘ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰው ከመተላለፉ በፊት ሌሎች እንስሳቶች እንደ መካከለኛ የቫይረሱ አስተላላፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ቫይረስ በእንስሳት ውስጥ ከመተንፈሻ አካላት በሽታ በተጨማሪ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ በሽታን ያስከትላል ይሁንና በሰዎች ውስጥ ከቀላል ህመም እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመም ያሉ በሽታዎችን የሚያስከትል ነው፡፡ ሌሎች የኮሮና ቫይረስ አይነቶች ውስጥ ሳርስ ኮቭ (SARS-COV) እና መርስ ኮቭ (MERS-COV) በመባል የሚታወቁ ቫይረሶች ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ ቫይረሶች ሳርስ በ 2002 እ.ኤ.አ እና መርስ በ2012 እ.ኤ.አ ብዙ ሰዎችን የያዘ ወረርሽኝ አስከትለው አልፈዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ከውሃን ከተማ፣ ሁቤይ ክፍለ ሀገር፣ ቻይና መንስኤው ያልታወቀ የሳንባ ምች ህሙማን እንደነበራቸው በታህሳስ 21፣ 2012 ዓ.ም ለዓለም ጤና ድርጅት አሳውቀዋል፡፡ ይሁንና ቫይረሱ ከቻይና አልፎ ሌሎች ሀገራት ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ብዙ ሰዎችን ከመያዛቸውም በላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕብረተሰብ ጤና አሳሳቢ ችግር መሆኑን በጥር 21፣ 2012 ዓ.ም አውጇል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቫይረሱ በብዙ ሀገራት ውስጥ በመሰራጨቱና ብዙ ህዝብን በመያዙ የዓለም የጤና ድርጅት በመጋቢት 2፣2012 ዓ.ም በሽታውን የዓለም ወረርሽኝ (pandemic) እንደሆነ አውጇል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥር 18፣ 2012 ዓ.ም ጅምሮ ለኮቪድ-19 የድንገተኛ ጊዜ ዝግጅት እና ምላሽ ማስተባበሪያ ማእከል በማቋቋም ለበሽታው ቁጥጥር ውጤታማነት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታ የመጀመሪያው በበሽታው መያዙ የተረጋገጠ ሰው በመጋቢት 3፣ 2012 ዓ.ም ሪፖርት ተደርጓል፡፡